የኮንሶ ምሁራን ማህበር(#KIA) አባላት በተማሩበት ሙያ ማህበረሰቡን ለማገልገል በትጋት እየሰሩ መሆኑ ተገለጸ፤







የኮንሶ ምሁራን ማህበር(#KIA) አባላት በተማሩበት ሙያ ማህበረሰቡን ለማገልገል በትጋት እየሰሩ መሆኑ ተገለጸ፤
በኮንሶ ምሁራን ማህበር ቦርድ ፀሐፊና የአ/ም ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር ኢንጂነር አያኖ ህርቦ ተዘጋጅቶ «#Wings_of_Healing #Ethiopia» በሚባል ድርጅት የገንዘብ ድጋፍ በኮንሶ ዞን ሁለት ወረዳዎችና በካራት ከተማ አስተዳደር የሚተገበረው የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ፕሮጀክት፣ አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ እያጠናቀቀ መሆኑ ተገለጸ።
በፕሮጀክቱ አስተባባሪ ኢንጂነር ሳምሶን በኮ እና በዶ/ር ኢንጂነር አያኖ ህርቦ አማካኝነት ተግባራዊ የሚሆነው ይህ ፕሮጀክት፤ በኮንሶ ዞን #ሰገን ዙሪያ ወረዳ በተመረጡ ሁለት ቀበሌዎች እንዲሁም #በከና ወረዳ በተመረጡ ሁለት ቀበሌዎች የውሃ ቦኖዎችን የመገንባትና የውሃ ምንጮችን የማጎልበት ሥራዎችን እንደሚያከናውን ታውቋል።
በተጨማሪም #በካራት_ከተማ በመንግሥት የተገነባው የውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳ 100 ሜትር ኩብ ብቻ የሚይዝ በመሆኑና ለከተማው ማህበረሰብ በቂ ባለመሆኑ፣ 500 ሜትር ኩብ የሚይዝ ተጨማሪ የውሃ #ገንዳ በትብብር ለመገንባት ዕቅድ መያዙ ተገልጿል።
በቀጣይ እነዚህን ሁነኛ የልማት ሥራዎች እውን ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ስምምነት ላይ በመድረስ፣ ፕሮጀክቱ #በዚህ #ዓመት ውስጥ ሙሉ በሙሉ #እንደሚጠናቀቅ ተመላክቷል።
ሐሳባቸውን ያጋሩት የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ኢንጂነር ሳምሶን በኮ፤ «ዶ/ር ኢንጂነር አያኖ ህርቦን ሳስብ ከሁሉም በላይ የሚያስደንቀኝና የሚያነሳሳኝ ትህትናው፣ እንዲሁም ምንም ዓይነት ጥቅም ሳይጠብቅ እውቀቱን፣ ጊዜውንና ልምዱን ማህበረሰቡ ንጹህ ውሃ እንዲያገኝ ለመርዳት ያለው ቀናነትና ቁርጠኝነት ነው። ዛሬ በተባረኩ አጋሮች ለጋስ ድጋፍ ለማህበረሰባችን ዘላቂ የንጹህ ውሃ አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ አብረን እየሠራን እንገኛለን። ውድ ወዳጄ አያኖ፤ ያንተ ቁርጠኝነት እውነተኛ ስኬት የሚለካው ባገኘነው ውጤት ብቻ ሳይሆን ሌሎችን በምናገለግልበት መንገድ መሆኑን ያስታውሰናል።» ሲሉ ገልጸዋል።
ዶ/ር ኢንጂነር አያኖ ህርቦ በበኩላቸው፤ «ኢንጂነር ሳምሶን በኮ፣ ለረጅም ጊዜ በዘለቀው ወዳጅነታችን እንዲሁም ዘላቂ የንጹህ ውሃ አቅርቦትን በማረጋገጥና የኑሮ ደረጃን በማሻሻል ማህበረሰባችንን ለመለወጥ አብረን ለመሥራት ባገኘነው ዕድል እኮራለሁ። #ሙያዊ_እውቀት፣ እውነተኛ አጋርነት እና የህዝብ አገልጋይነት የጋራ ቁርጠኝነት በአንድ ላይ ሲጣመሩ ለአሁኑም ሆነ ለመጪው ትውልድ ዘላቂ የሆነ ለውጥ መፍጠር እንደምንችል ጽኑ እምነት አለኝ።» በማለት አጋርነታቸውንና እምነታቸውን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ዶ/ር ኢንጂነር አያኖ ህርቦ ከዚህ ቀደም ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በካራት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ #የውሃ_ገንዳ እንዲገነባ ማድረጋቸውና ከኮንሶ ምሁራን ማህበር (#KIA) ጋር በመተባበር አጠቃላይ የኮንሶ #ከርሰ_ምድር_ውሃ ጥናት ማካሄዳቸው የሚታወስ ነው።
በተለይም የኮንሶ ምሁራን ማህበር (#KIA) ያደረገው የከርሰ ምድር ውሃ ጥናት #ለዚህ_ዕድል_መሠረት መጣሉ የታወቀ ሲሆን፣ አሁን የተጀመረው አዲሱ ፕሮጀክት ለዞኑ ማህበረሰብ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
#የኮንሶ_ምሁራን_ማህበርም ምሁራን በተማሩበት መስክ ተሰባስበው የማህበረሰባቸውን ችግር ለመቅረፍ የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ የማድረግ ሥራውን አጠናክሮ ይቀጥላል።



Comments