top of page
Search

የኮንሶ ምሁራን ማህበር 4ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በደማቅ ሁኔታ እየተካሄደ ነው!


የኮንሶ ምሁራን ማህበር 4ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በደማቅ ሁኔታ እየተካሄደ ነው!


“INKOLADEY, MAANAN SAMYTA KODA?” በሚል መሪ ቃል የኮንሶ ምሁራን ማህበር (KIA) 4ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በኮንሶ ካራት በደማቅ ሁኔታ እየተካሄደ ይገኛል።


ጉባኤው በኮንሶ ባህላዊ ኪነ-ጥበብና ጭፈራ እንዲሁም በአባቶች ቡራኬ የተጀመረ ሲሆን፣ የማህበሩ ሰብሳቢ አቶ ጉማቸው ኩሴ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።


አቶ ጉማቸው በመልዕክታቸው፣ የኮንሶ ምሁራን ማህበር ለኮንሶ ህዝብ ለውጥ የጋራ ሀሳብና ዓላማ ይዞ እየሰራ ያለ ማህበር መሆኑን ገልጸው፤ ለውጥ በአንድ ጀምበር እንደማይመጣ በመጠቆም፣ ማህበሩ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በጥናትና ምርምር የተደገፉ ስራዎችን በማከናወን የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን አስረድተዋል።


የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ክቡር አቶ ገለቦ ጎልቶሞ በጉባኤው ባስተላለፉት መልዕክት፣ የምሁራን ማህበሩ በተቀናጀ መንገድ ለህዝባችን የተወሳሰቡ ችግሮች በጥናትና ምርምር ላይ የተመሠረቱ መፍትሄዎችን ማቅረብ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

በተለይም በኮንሶ የትምህርት ዘርፍ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ የባህላዊ እሴቶች ጥበቃ እና ሌሎች ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ምሁራን በያካበቱት ዕውቀት ሊያግዙ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

አፋ ኮንሶ የማንነታችን ዋነኛ መገለጫ በመሆኑ፣ ቋንቋችንን ለማሳደግና ለትውልድ ለማስተላለፍ በቅንጅት መረባረብ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።


በተጨማሪም፣ ምሁራን መሠረተ-እውነት በሌላቸው መረጃዎችና በበሬ ወለደ ወሬዎች ከመመራት ይልቅ፣ በምክንያታዊነትና በሳይንሳዊ ዕውቀት ችግር ፈቺ መፍትሄዎችን ለማፍለቅ መትጋት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።


የኢፌዴሪ ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ እና የኮንሶ ህዝብ ተወካይ ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ በበኩላቸው፣ የኮንሶ ማህበረሰብን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ለውጥ ለማምጣት ምሁራን፣ መንግስትና የግሉ ዘርፍ በተቀናጀ መልኩ መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።


ያሉንን የተፈጥሮና የሰው ሀብቶች ወደ ሀብት በመቀየር ለወጣቱ ትውልድ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሶስትዮሽ ትብብር ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።


የምሁራን ጥንካሬ የሚለካው በትውልድ ተሻጋሪ ተቋማትን በመገንባትና ለህዝብ ችግሮች በጋራ መፍትሄ በማፍለቅ መሆኑንም አስታውሰዋል።


በጉባኤው የጥናትና ምርምር ስራዎችም እየቀረቡ ይገኛሉ።

📌 በትምህርት ዘርፍ የተሰራ የጥናትና ምርምር ስራ በዶ/ር ሲቢሎ ጋሹሬ እየቀረበ ይገኛል።

📌 በከርሰ ምድር ውሃ ላይ የተሰራ የጥናትና ምርምር ስራ ደግሞ ከሰዓት በዶ/ር ኢንጂነር አያኖ ሂርቦ ይቀርባል።


በሲምፖዚየሙ ላይ ችግር ፈቺ ሀሳቦችን ለማፍለቅና ለኮንሶ ህዝብ ተጨባጭ መፍትሄዎችን ለማበጀት በሚያግዙ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ውይይቶች ይካሄዳሉ።


👉 ስለዚህ የኮንሶ ምሁራን ማህበር አባል የሆናችሁም ሆነ ያልሆናችሁ፣ ለኮንሶ ህዝብ ችግሮች መፍትሄ የሚያመጡ ሀሳቦች አሉኝ የምትሉ ሁሉም የኮንሶ ምሁራን የዛሬውን ሲምፖዚየም በመከታተል የሀሳብ አስተዋጽኦአችሁን እንድታደርጉ በአክብሮት እንጋብዛለን።

KIA | Knowledge • Research • Collaboration • Transformation

 
 
 

Comments


bottom of page