የኮንሶ ምሁራን ማህበር አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ከዋና ጽ/ቤት ጋር በመሆን 130ኛውን የዓድዋ ድል በዓል ምክንያት በማድረግ ከአጠቃላይ አባላቱና አዲስ አበባ ከሚኖሩ የኮንሶ ተወላጆች ጋር ያደረገው ውይይት በስከት ተጠናቀቀ።
- basire balcha
- 6 days ago
- 2 min read
የኮንሶ ምሁራን ማህበር አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ከዋና ጽ/ቤት ጋር በመሆን 130ኛውን የዓድዋ ድል በዓል ምክንያት በማድረግ ከአጠቃላይ አባላቱና አዲስ አበባ ከሚኖሩ የኮንሶ ተወላጆች ጋር ያደረገው ውይይት በስከት ተጠናቀቀ።















የውይይቱ ዋና ዓላማ ጀግኖች አባቶቻችን ዘመናዊ መሳሪያ ታጥቆ በሀገራችን ላይ ወረራ ለመፈፀም የመጣውን ወራሪ ኃይል ድባቅ መትተው አንገት በማስደፋት ወደ መጣበት መመለስ የቻሉት፣ ልዩነቶቻቸውን በማጥበብና የውስጥ አንድነታቸውን በማጠናከር በእጃቸው የነበረውን ጥቂት መሣሪያ ከታላቅ ብልሃትና ጥልቅ የሀገር ፍቅር ጋር አቀናጅተው በመታጠቃቸው በመሆኑ፣ እኛ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ያለን የኮንሶ ምሁራን እኛን አስተምሮ ለቁም ነገር ያበቃው ታታሪው የኮንሶ ህዝብን ዘቅሰው ከያዙት ዘርፈ ብዙ ችግሮች አላቀን ማሻገር የምንችለው እንደ አድዋ ጀግኖች ሁሉ፣ ልዩነቶቻችንን አስወግደን፣ ከመጠላላት፣ ከመፈራረጅና ከመጠላለፍ አዙሪት ወጥተን የህዝባችንን መብትና ጥቅም ለማስከበር በአንድነት መቆም ስንችል ብቻ በመሆኑ፣ ምሁራን ህዝባችንና ሀገራችንን የሚያሻግር ሀሳብ በማፍለቅ ሰላሚዊ፣ የተለወጠና የበለፀገ የኮንሶ ማህበረሰብ ለማየት ያነገብነውን ራዕይ ዕውን ለማድረግ በውስጣችን ያለውን እምቅ አቅምና ዕውቀት አሟጠን መጠቀም ጊዜው የሚጠይቀው ወሳኝ ጉዳይ በመሆኑ ነው።
የውይይት መድረኩን የመሩት የአዲስ አበባ የቅርንጫፍ አስተባባሪዎች የሆኑት ቄስ ደጉ ገንፌ፣ አማኑኤል ኮራ እና በቀለ በርሻ ሲሆኑ የኮንሶ ምሁራን ማህበር ሰብሳቢ አቶ ጉማቸው ኩሴ የኮንሶ ምሁራን ማህበር አመሰራረት፣ ማንነትና ማህበሩ እስካሁን የሰራቸው ስራዎችን በማስመልከት ለተሰብሳቢዎች ገለፃ አድርገዋል።
ገለፃውን ተከትሎ የውይይቱ ተሳታፊዎች በርካታ አስተያየቶችና ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን የማህበሩ ቦርድ ሰብሳቢዶ/ር አማኑኤል ኩሲያ፣ የማህበሩ የሀሳብ አመንጭ ቡድን ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ማቲዎስ ገለቦ፣ የማህበሩ ቦርድ አባል አስቻለው ኮራ እና የማህበሩ ስራ አስኪያጅ ባስሬ ባልቻ ከአባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ሰፊ ምላሽና ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል።
የኮንሶ ምሁራን ማህበር ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት ዶ/ር አማኑኤል ኩሲያ ከዚህ ቀደም የኮንሶ ምሁራን ተከፋፍለው መንገድ ላይ ሰላም መባባል እንኳን የማይታሰብበት ወቅት እንደነበረ በማስታወስ፣ በውይይቱ ላይ በርካታ የኮንሶ ልጆች ተገኝተው የአድዋ ድል በሚከበርበት ቀን ስለኮንሶ ህዝብ አንድነት፣ ሰላምና ልማት ለመወያየት መብቃታቸው በራሱ ትልቅ ስከት መሆኑን በመግለፅ፣ ማህበሩ የኮንሶ ህዝብ በከፍተኛ ጭንቅ ውስጥ በነበረበት ህዝባችንን ለማሻገር በዛ ጭንቅ ውስጥ የተወለደ መሆኑን በመግለፅ፣ አይደለም በዚህ ጭንቅ ውስጥ የተወለደው ማህበራችን የትኛውም ተቋም ሲመሰረት የራሱ የሆነ ተፈጥሯዊ የዕድገት ደረጃዎች ያሉት መሆኑን በአፅንኦት ገልፀው፣ ህፃን ልጅ ሲወለድ ሮጠህ ይህን አምጣ ከማለት በፊት በብዙ እንክብካቤ ማሳደግና መንከባከብ እንደሚያስፈልግ ሁሉ የኮንሶ ምሁራን ማህበርም እንደ ተቋም ከተመሰረተ ማግስት ህዝቡ ከፍተኛ ችግር ውስጥ የነበረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወዲያው ሁሉንም ችግር ብቻውን እንደሚፈታ የሚጠብቁ በርካቶች መኖራቸው ባያስገርምም ነገር ግን ተቋሙ እስካሁን ግቡን ለማሳካት ከሚጠበቀው በላይ መስራቱን አብራርተዋል።
የኮንሶ ምሁራን ማህበር መስራች አባል፣ በኢፌዲሪ ህ/ተ/ም/ቤት የኮንሶ ህዝብ ተወካይና የስራና ክህሎት ሚንስቴር ሚንስትር ዴኤታ የተከበሩ አቶ ሰለሞን ሶካ በውይይቱ ላይ ተገኝተው ለውይይቱ ተሳታፊዎች መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን በመልዕክታቸውም የኮንሶ ምሁራን ማህበር ሲመሰረት የኮንሶ ህዝብ እንደህዝብ በጎራ ተከፋፍሎ ከየአቅጣጫው ጦርነት ተከፍቶበት በርካታ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ሲያስተናግድ በነበረበት የጭንቅ ሰዓት መሆኑን በማስታወስ ያኔ ለህዝባችን ህሊውና ሲባል ሁሉንም ነገር ይቅር ተባብለን እንደ አድዋ ጀግኖች አባቶቻችን አንድ ላይ ቆመን ህዝባችንን ለመሻገር ባንሰራ ኖሮ አሁን ላይ እያየን ያለነው አንፃራዊ ውስጣዊ ሰላምና አንድነት ማምጣት አይቻልም ነበር ብለዋል። ቀጥለውም የሀሳብ ልዩነቶች ተፈጥሯዊ በመሆናቸው እንደ ፀጋ ቆጥረን በሚያግባቡንና የጋራ በሆኑ የህዝብ አጀንዳዎች ላይ ያለ ልዩነት በአንድነት ቆመን ህዝባችንን ማሳረፍ ይጠበቅብናል በማለት ማህበሩ ከተመሰረተ በ3 ዓመት ውስጥ የሰራቸው በርካታ ስራዎችን በማድነቅ በቀጣይ ማህበሩ በህዝቡ ሰላም፣ አንድነትና ልማት ላይ የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንድቀጥል ምክራቸውን ለግሰዋል።
በውይይቱ የኮንሶ ምሁራን ማህበር ሰብሳቢ አቶ ጉማቸው ኩሴ፣ የማህበሩ ቦርድ ሰብሳቢና የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዩንቨሪሲቲ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አማኑኤል ኩሲያ እና የማህበሩ ዋና ስራ አስኪያጅ ባስሬ ባልቻን ጨምሮ ሌሎች የማህበሩ ቦርድ አባላት፣ የስልታዊ እቅድ አስፈፃሚ ቡድን አስተባባሪዎችና የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ አስተባባሪዎች እንዲሁም የማህበሩ አባላትና በአዲስ አበባ የሚኖሩ የኮንሶ ተወላጆች ተገኝተዋል።
የኮንሶ ምሁራን ማህበር (KIA)
የካቲት 23/ 2018 ዓ.ም



Comments