የኮንሶ ምሁራን ማህበር (KIA) ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የፕሮጀክተር እና የካዝና (safe box) ድጋፍ ተበረከተለት።
- Tegegne Tesfaye
- May 6
- 2 min read
የኮንሶ ምሁራን ማህበር (KIA) ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የፕሮጀክተር እና የካዝና (safe box) ድጋፍ ተበረከተለት።
የኮንሶ ምሁራን ማህበር "ሰላማዊ፣ የተለወጠና የበለፀገ የኮንሶ ማህበረሰብን ማየት" የሚል ራዕይ አንግቦ ግንቦት 21 ቀን 2015 ዓ.ም ህጋዊ ሰውነት አግኝቶ በይፋ ከተመሰረተ ገና 2 ዓመት ያልሞላው ቢሆንም ማህበሩ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ አደረጃጀቱን ዘርግቶ በመላው ዓለም የሚገኙ የኮንሶ ምሁራንን በማሰባሰብ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮችን ከማድረግ ባሻገር የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅና ለከፍተኛ አመራርና ሰራተኞች የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት በርካታ ስራዎችን በማከናወን ላይ የሚገኝ በመሆኑ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ማህበሩ ህግና መመሪያዎችን መሰረት በማድረግ ከተመሰረተ በአጭር ጊዜ ውስጥ እያስመዘገበ ላለው አመርቂ ውጤት እውቅና በመስጠት ማህበሩ እያስመዘገበ ያለውን ውጤት አጠናክሮ መቀጠል እንድችል የፕሮጀግተርና የጋዝና ድጋፍ አበርክቶለታል። ድጋፉንም የኮንሶ ምሁራን ማህበር ሰብሳቢ አቶ ጉማቸው ኩሴ እና የማህበሩ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ባስሬ ባልቻ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እጅ ተረክበዋል።
የኮንሶ ምሁራን ማህበር ሀገር በቀል የበጎ አድራጎት ማህበር ሲሆን ዓላዎቹም፦
1. የማህበረሰቡ የትምህርት፣ የጤና፣ የግብርናና የንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና አገልግሎት አሰጣጥ፣ የመልካም አስተዳደር እና በቁልፍ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ዙሪያ ጥናትና ምርምሮችን ማድረግ፤
2. የማህበረሰቡ ልማትና ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለማሳደግ ፕሮጀክቶችን መቅረጽና የራሱን አስተዋፅኦ ማበርከት፤
3. የማህበረሰቡ ባህልና ቋንቋ ለማልማትና ለማሳደግ ምሁራዊ አስተዋፅኦ በማበርከት ከባለድርሻ አካላት ጋር መስራት፤
4. በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ የማህቀረሰብ ክፍሎችን መደገፍ፤
5. የአከባቢው የንግድ ማህበረሰብና የሙያ ማህበራትን መደገፍ፤
6. የአከባቢው ማህበረሰብ ሁለንተናዊ ዕድገትና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክሮችን ማድረግ፤
7. በሀገር ውስጥና በመላው ዓለም የሚኖሩ የማህበረሰቡ ተወላጆች ህብረት ፈጥረው በዕውቀታቸውና በሙያቸው ማህበረሰቡን ማገልገል እንዲችሉ ምቹ መድረክ መፍጠር፤
8. ማህበረሰቡ የእራሱ በሆኑ ሀገር በቀል ዕሴቶች እና የመንግስት አስተዳደር ሥርዓት ላይ ያለው ንቃተ ህሊና እንድዳብር ማገዝ፤
9. ለአከባቢው ማህበረሰብ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ማስተዋወቅና በአግባቡ መጠቀም እንዲችል መደገፍ፤
10. ተማሪዎች በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ማስመዝገብ እንዲችሉ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግና የማበረታቻ ሥርዓት መዘርጋት፤ እንዲሁም ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውና የፈጠራ ሀሳብ(ሥራ) የሚያመነጩ(የሚሰሩ) ተማሪዎችና ወጣትችን ማበረታታት፤
11. ከአጎራባች ማህበረሰቦች ምሁራን ጋር ግንኙነት በመፍጠር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና ትብብርን ማጠናከር ለዘላቂ ልማትና ሰላም በጋራ መሥራት፤
12. የአከባቢው ማህበረሰብ ሁለንተናዊ ዕድገት ለመደገፍ የተለያዩ ፎረሞችን ማቋቋም፤
13. በአከባቢያዊ፣ ክልላዊ እና ሀገራዊ የሰላም፣ ልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ላይ በንቃትና በተደራጀ መልኩ መሳተፍና የኮንሶ ማህበረሰብ ልምድ በመቀመርና በማካፈል የበኩሉን ሙያዊ አስተዋፅኦ ማበርከት የሚሉ ናቸው።
በመሆኑም ማህበራችን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ላደረገለት ድጋፍ ልባዊ ምስጋናውን እያቀረበ፣ ማህበሩ (KIA) ከኮንሶ ህዝብ በወጡ ምሁራን ለኮንሶ ህዝብ የተቋቋመ እና የማህበረሰቡን ችግሮች ለመቅረፍ ግልጽ ዓላማዎችና ራዕይ አንግቦ ህግና ስርዓትን ተከትሎ የሚንቀሳቀስ ማህበር በመሆኑ በቀጣይ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብና ራዕዩ እውን እንዲሆን ጠንክሮ የሚሰራ መሆኑንም በዚህው አጋጣሚ እየገለፀ፣ አንዳንድ ግለሰቦች ኮሽ ባለቁጥር ከመሬት ተነስተው ያለምንም መረጃና ማስረጃ በማህበራዊ ሚዲያዎች የማህበራችንን ስም የማጠልሸትና ከፖለቲካ ጋር ለማያያዝ ከሚያደርጉት እኩይ ተግባር እንዲታቀቡ በዚህ አጋጣሚ ማሳሰብ ይወዳል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ግለሰቦቹ በዚህ እኩይ ድርጊታቸው የሚቀጥሉ ከሆነ ግን ማህበሩ በርካታ የህግ ምሁራን አባላት ያሉት ማህበር እንደመሆኑ እነዚህን ግለሰቦች የማይታገስና በህግ አግባብ ለመጠየቅ የሚገደድ መሆኑን እየገለፀ ከወዲሁ አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግ ያሳስባል።
ሰላማዊ፣ የተለወጠና የበለፀገ የኮንሶ ማህበረሰብ ለማየት ተግተን እንሰራለን!!
የኮንሶ ምሁራን ማህበር!
ሚያዝያ 27/2017 ዓ.ም
Comentarios