#ከኮንሶ_ምሁራን_ማህበር_የተሰጠ_መግለጫ!
- Tegegne Tesfaye
- May 8
- 4 min read
ከኮንሶ_ምሁራን_ማህበር_የተሰጠ_መግለጫ
የኮንሶ ምሁራን ማህበር "ሰላማዊ፣ የተለወጠና የበለፀገ የኮንሶ ማህበረሰብን ማየት" የሚል ራዕይ አንግቦ በአዋጅ ቁጥር 1113/2011 መሰረት ግንቦት 21 ቀን 2015 ዓ.ም በኢፌዴሪ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ተመዝግቦ ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ በይፋ የተመሰረተ የበጎ አድራጎት ማህበር ነው፡፡
ማህበሩ ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ በይፋ ከተመሰረተ ጀምሮ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ በተለያዩ የሀገራችንና የዓለማችን ክፍሎች የተሰማሩ ሁሉም የኮንሶ ምሁራን በማህበሩ ጥላ ስር በመሰባሰብ የወጡበትን የኮንሶ ማህበረሰብ ማገልገል እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በሀገር ውስጥና እና በውጭ ሀገራት የተለያዩ ቅርንጫፎችን ዘርግቶ ዋና ትኩረቱን በኮንሶ ህዝብ ‘’ሰላም፣ ለውጥና ዕድገት’’ ላይ በማድረግ እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ በሺህ የሚቆጠሩ የኮንሶ ምሁራንን በማሰባሰብ ችግር ፈቺ የሆኑ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን የማካሄድ፣ የኮንሶ ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን የመቅረጽና እና የተለያዩ ሥልጠናዎችን አዘጋጅቶ ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ሲሰጥ ቆይቷል፤ ለወደፊትም እነዚህን ተግባራት አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
ይሁንና ከማህበሩ ምስረታ አንስቶ አስቀድሞም የኮንሶ ህዝብን በመከፋፈልና አንድነት እንዳይኖረው በማድረግ ዓለም የመሰከረለት ታታሪውና ሰላም ወዳዱን የኮንሶ ህዝብ በጎ ስም በማጠልሸትና መልካም ዕሴቶቹን በመሸርሸር ብሎም ኢኮኖሚውን በማድቀቅ ህዝባችንን አንገት ለማስደፋት ሲሰሩ የከረሙ አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች የኮንሶ ምሁራን በማህበር መደራጀት ብቻ ሳይሆን የማህበሩ ራዕይ፣ ዓላማዎች እና በጎ እንቅስቃሴዎች ስላልተዋጠላቸው ከኋላ ሆነው የሚዘውሯቸው ተላላኪ ቅጥረኞችን በማሰማራትና ሀሰተኛ የፌስቡክ አካውንቶችን(fake facebook accounts) በመጠቀም ይህ ትልቅ ዓላማ ሰንቆ የተነሳውና ከተቋቋመ ገና ሁለት ዓመት ያልሞላው የኮንሶ ምሁራን ማህበርን መልካም ስም በየጊዜው እየፈበረኩ በሚያሰራጩት ሀሰተኛ መረጃዎች ሲያጎድፉትና ሲያጠለሹ ቆይተዋል፡፡
እነዚህ አካላት የኮንሶ ምሁራን ማህበር መልካም ስም በማጉደፍና በማጠልሸት ላይ ብቻ ሳይወሰኑ ለኮንሶ ህዝብ የተሻለ ህይወት ለትተቀን የሚተጉ እንደ#ኮንሶ_ልማት_ማህበር ያሉ ህዝባዊ የልማት ተቋማትን እና የተለያዩ ግለሰቦችን (በተለይ #ታዋቂ_የኮንሶ_ምሁራንን) መልካም ስም ባልተገባ መንገድ በማንሳትና በማንኳሰስ ላይ ተሰማርተዋል፡፡ በየጊዜው አቀነባብረው በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በሚለቋቸው የተዛቡ ሀሰተኛ መረጃዎችም በህዝብ መካከል ውዥንብር እንዲፈጠርና እርስ በርስ መተማመን እንዳይኖር እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
የኮንሶ ምሁራን ማህበር በየትኛውም አካል የተመዘበረ የመንግስትና የህዝብ ገንዘብና ንብረት፣ እንዲሁም በህዝቡ ላይ የሚደርሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ቢኖሩ በጽኑ የሚያወግዝ ብቻ ሳይሆን በእነዚህ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ወይም የሚሰማሩ አካላት ላይ ህጋዊ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ከሚመለከታቸው የአስተዳደርና የፍትህ አካላት ጋር በትብብር ይሰራል፡፡
ነገር ግን ከዚህ ባፈነገጠ መልኩ አንዳንድ ግለሰቦችና ሀሰተኛ የፌስቡክ ማንነት የሚጠቀሙ ቅጥረኞች ራሳቸውን ‘’የማህበረሰብ አንቂዎችና ተቆርቋሪዎች’’ በማስመሰል የተለያዩ ሀሰተኛ መረጃዎችን እየፈበረኩ በማቀነባበር በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የመልቀቅ ተግባር ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡ ይህም ሁኔታ በህዝቡ ውስጥ አለመተማን እንዲፈጠርና ህዝባችን በአንድነት ቆሞ በልማቱ ላይ እንዳያተኩር ከማድረግ አኳያ የጎላ አሉታዊ ድርሻ እንዳለው ይታመናል፡፡
በዚህ አደገኛ ተግባር ላይ ከተሰማሩ አካላት መካከልም ራሱን “#የገበያ_መረጃ’’ በሚል ሀሰተኛ የፌስቡክ ማንነት(አካውንት) የሚጠቀመው ግለሰብ/ቡድን ይገኝበታል፡፡ ይህ የሀሰተኛ የፌስቡክ አካዉንት ተጠቃሚ ግለሰብ/ቡድን በቅርቡ በተጠረጠረበት ወንጀል በአዲስ አበባ ከተማ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ከተነገረው ‘’የቀድሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ረዳት የመንግስት ተጠሪ እና የአሁኑ የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ጉዳይን እንደምቹ አጋጣሚ በመጠቀም፤ ከጉዳዩ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌለውና ከማንኛውም ፖለቲካዊ ጉዳዮች ነፃ በመሆን የኮንሶ ህዝብን ከድህነት አረንቋ ነፃ በማውጣትና ወደ ብልጽግና ማማ ለማሻገር ግልፅ ዓላማዎች አንግቦ በሕጋዊ መንገድ የተቋቋመውን የኮንሶ ምሁራን ማህበርን በአሳፋሪ ሁኔታ ከጉዳዩ ጋር ለማገናኘት በመሞከር የማህበራችንን መልካም ስም ለማልጠሸትና ለማጉደፍ ሲውተረተሩ ተመልክተናል፡፡
እነዚህ ከጅምሩ በኮንሶ ምሁራን ማህበር ላይ በመዝመት መፍረሱን እየተመኙ ያሉ የኮንሶ ጠላቶች ተላላኪ ግለሰቦችና ቡድኖች በዋናነት ይህ በመላው የኮንሶ ምሁራን ተመስርቶ በትላልቅ ምሁራን የሚመራ የበጎ አድራጎት ማህበር በምንም ዓይነት ሁኔታ የፖለቲካ ሸፍጥ ማስፈጸሚያ መሳሪያ ሊሆን እንደማይችል ጠፍቷቸው ሳይሆን የኮንሶ ምሁራን አንድ ላይ ከተሰባሰቡ እስከ ዛሬ ድረስ የኮንሶ ህዝብን እርስበርሱ በመከፋፈል የኮንሶ ህዝብ ሁለንተናዊ ጥቅሞችን ወደ ሌላ ቦታ በማሸሽ ህዝባችን አንገት ደፍቶ በድህነት እየማቀቀ እንዲኖር የነደፉት እኩይ ሴራ ያከሽፉብናል ከሚል ፍርሃት እንጂ ለኮንሶ ህዝብ ተቆርቁረው እንዳልሆነ እኛ ብቻ ሳንሆን ህዝባችንም በሚገባ ይገነዘባል፡፡ የኮንሶ ምሁራን ማህበር ለኮንሶ ህዝብ ምን ማለት እንደሆነም መላው ህዝባችን ጠንቅቆ ያውቀዋል፡፡ ለዚህም ነው ከደቂቅ እስከ ሊቅ ”kirrittaa Xonso A’kutuumaa K’ee haa KIA”እያለ የሚያዘመው!!!
በተለይም ይህ #የገበያ_መረጃ በሚል ሀሰተኛ የፌስ ቡክ ገፅ የሚጠቀመው ቅጥረኛ ግለሰብ/ቡድን ሚያዝያ 25 ቀን 2017 ዓ.ም ከባህላችን ያፈነገጠ ብቻ ሳይሆን ፍፁም ኢ-ሞራላዊና ክብረነክ በሆኑ ፀያፍ ቃላት የታጨቀ፣ እጅግ በጣም ነውረኛ በሆኑ የስድብ ቃላት የታጨቁ አደገኛ የሀሰተኛ መረጃዎችን ከቆሸሸ ጭንቅላቱ ፌብርኮ በማህበራዊ ሚዲያ ያሰራጨ ሲሆን የኮንሶ ምሁራን ማህበርንን ‘’የሌቦች ጉዳይ አስፈፃሚ‘’ አድርጎ ከመሳል አልፎ ማህበሩ መፍረስ አለበት እስከማለት ደርሷል፡፡ ከዚህም አልፎ ማህበራችን እዚህ ላይ መግለፅ በማይችላቸው እጅግ ፀያፍ ቃላት የኮንሶ ምሁራን ማህበርን ብቻ ሳይሆን የኮንሶ ህዝብ ተወካዮችንም እስከመዝለፍ ሄዶ እጅግ አስነዋሪና እጅግ አደገኛ የሆነ ሀሰተኛና የጥላቻ መረጃን በማህበራዊ ትስስር ገጹ ላይ በማጋራት በማህበሩ ላይ የጥላቻ ዘመቻ ከፍቷል፡፡ አንዳንድ በስም የሚታወቁ ግለሰቦችም ጭምር እጅግ በጣም አሳፋሪ በሆነ መልኩ በራሳቸው የፌስ ቡክ ገፆች ላይም ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ሀሰተኛና የጥላቻ መረጃዎችን አስፍረው ተመልክተናል ፡፡
በመሆኑም የኮንሶ ምሁራን ማህበር በማንኛውም አካል ተቀነባብረው የሚሰራጩ ሀሰተኛና የጥላቻ መረጃዎችንበጽኑ እያወገዘ፤ 1. በአንደዚህ ዓይነት ተግባራት ላይ የተሰማሩ አካላትን የጥላቻ ንግግር እና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1185/2012 አንቀፅ 2(2)፣ 4 እና 7 ንመሰረት ተጠያቂነትን የሚያመጣ እና ወንጀል እንደሆነ ያስገነዝባል፣ በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ማንነት የመለየትና በህግ ጭምር እንዲጠየቁ የማድረግ ሥራዎችን ይሰራል።2. መላው የኮንሶ ምሁራንና ህዝብ የሀሰተኛ ማንነት ባላቸው የተለያዩ አካላት ተቀነባብረው በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚለቀቁ ሀሰተኛ መረጃዎችን ትክክለኛነት ሳያረጋግጡ ከማጋራት እና በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን ከመከተል እንዲቆጠቡ አበክረን ለማሳሰብ እንወዳለን፣ አብዛኞቹ ሀሰተኛ ገፆች በኮንሶ ስሞች ይከፈቱ እንጂ የሚጠቀሙባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ከጥቂት ለሆዳቸው ካደሩ ቅጥረኛ የኮንሶ ተወላጆች በስተቀር ከኮንሶ ውጭ ያሉ፣ የኮንሶ ሰላምና አንድነት የማይፈልጉ ሃይሎች የኮንሶ ህዝብን መልካም ስምና ክብር ለማጉደፍ እንደሚጠቀሙባቸው መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡3. የኮንሶ ዞን አስተዳደርና እና ሌሎች የሚመለከታቸው የፍትህ አካላት በህዝቡ ውስጥ የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች በህዝብ መካከል ሊፈጥሩ የሚችሉትን ውዥንብርና አለመተማመን እንዳይፈጥሩ መረጃዎቹን በንቃት በመከታተልና የህዝቡን ንቃተ ህሊና የማሳደግ ሥራዎችን አጠናክሮ እንዲሰራ እንመክራለን፡፡4. በአጠቃላይ የኮንሶ ምሁራን ማህበር የራሱን መልካም ስም በማጉደፍና እና በህዝቡ ውስጥ ሀሰተኛና የጥላቻ መረጃዎችን በማሰራጨት ላይ የተሰማራ ማንኛውም አካል በጽኑ ያወግዛል፣ አጥብቆም ይቃወማል፡፡ አለፍ ስልም በህግ እንዲጠየቁ ይሰራል!!!5. በመጨረሻም ታታሪነትህነ ዓለም የመሰከረልህ የተከበርከው ጀግናው የኮንሶ ህዝብ ሆይ! እውነተኛና ትክክለኛ መረጃዎችን ከሚታወቁ ታማኝ ምንጮች ብቻ በመጠቀም የጠነሰሱልህ የጥፋት ሴራ እንዳይታወቅባቸው ማንነታቸውን ደብቀው ላንተ የሚቆረቆሩ መስለው ከባህልህ ባፈነገጠ መልኩ መልካም ስምህና ክብርህና በአደባበይ በማጉደፍ ላይ የተሰማሩ የግል ጥቅም አሳዳጅ ተላላኪ ቅጥረኞችና ላኪዎቻቸው ለሚያሰራጩት የሀሰት ትርክቶች ጆሮ ዳባ በማለት የጥፋት ሴራቸውን እንዲታከሽፍ አጠብቀን እያሳሰብን እኛ ከአብራክህ የወጣን ውድ ልጆችህ የመሰረትንልህ የኮንሶ ምሁራን ማህበር ያለምንም ማወላወል አቅሙ በፈቀደ መጠን በታማኝነትና በጽናት ሰላምህን ለማፅናትና ብልፅግናናን ለማረጋገጥ የጀመርናቸው የልማትና የእውቀት ብርሃን ስርጭት ስራዎችን በማጠናከር በሙሉ አቅማችን ከጎንህ እንደሚንቆም በድጋሚ ለማረጋገጥ እንወዳለን።
Comments