top of page
Search

ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ማህበረሰብ መልማት የሚችለው እንደት ነው?


ኢትዮጵያ ውስጥ ልማት የሚመጣው ጠንክሮ በመስራት ብቻ ቢሆን ኖሮ፣ በዓለም ደረጃ በታታሪነቱ የሚታወቀው እና የታታሪነት ተምሳሌት የሆነው የኮንሶ ህዝብ ከማንኛውም አካባቢ በላይ ወይም ባላነሰ በራሱ አካባቢ ልማት ማረጋገጥ በቻለ ነበር።


ነገር ግን እውነቱ ይህ አይደለም፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የተስፋፋው ኢ-ፍትሐዊነት፣ ያልተመጣጠነ የሀብት ክፍፍል እና በየደረጃው ባለው የመንግስት የስልጣን መዋቅሮች ውስጥ ያለው የጥቅም ሰንሰለት በልማት ሂደት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል።


በመሆኑም ኢትዮጵያ ውስጥ ልማት የሚገኘው በስራ ብቻ ሳይሆን፣

👉የህዝብን ጥቅም የሚወክሉና የሚያስከብሩ አመራሮችን በየደረጃው በመገንባት፣

👉ከሌሎች አጋሮች ጋር የህዝብ ጥቅምን ያማከለ ዲፕሎማሲ በመስራት፣

👉በመንግስታዊ ቢሮክራሲ ውስጥ ጠንካራ የተያያዘ መዋቅር (institutional networks) በመፍጠር፣

👉በፖለቲካዊ መድረኮች ላይ በንቃት በመሳተፍ እና

👉የውስጥ አንድነትን በማጠናከር ነው።


ኢ-ፍትሐዊነት በተንሰራፋበት ማህበረሰብ ውስጥ፣ በትንንሽ ልዩነቶች ላይ እርስ በርስ እየተጠላለፉ፣ የውስጥ አንድነትን መሸርሸር እና ከፖለቲካዊ መዳ መራቅ ማህበረሰብን ወደ “ተመልካች” ሚና ይገፋዋል፤ ከዛ ልማት ሌላ አካባቢ ሲሰራ የበይ ተመልካች ሆኖ የመቅረት ሁኔታ ይፈጠራል። የኮንሶ ህዝብ ለዘመናት ጠንክሮ እየሰራ፣ የእጅ ስራው ከራሱ አልፎ በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት ተመዝግቦ የሀገሩን ስም በዓለም እስከማስጠራት ደርሶ፣ አካባቢው ላይ አንድም የፌዴራል ፕሮጀግት ያልተገነባውና ማህበረሰቡ ከልማት የተገለለ በሚመስል ሁኔታ ሌላው ቀርቶ በዞኑ መቀመጫ ካራት ከተማ እንኳን ዉሃና መብራትን ጨምሮ ለአንድ የከተማ ዕድገት ወሳኝ የሆኑ መሰረተ ልማቶች ብርቅ የሆኑት ለዚህ ይመስላል።


እናም በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ሌላ አካባቢ የሚሰራውን ልማት እየተመለከቱ “የእኛስ?” ማለት ብቻውን በቂ አይሆንም ማለት ነው!ድርጅት፣ ኃይል፣ ተፅዕኖ፣ አንድነት እና ስትራቴጂ ያስፈልጋሉ።

ስለዚህ፦

👉 የውስጥ አንድነትህን አጠናክር፤

👉የህዝብ ጥቅምን የሚያገለግሉ አመራሮችን ለማፍራት ትጋ፤

👉አጋሮችህን በግልጽ በመለየት፤ ዲፕሎማሲህን አጠናክር፤

👉በፖለቲካ በንቃት ተሳተፍ፤

👉ጠንክረህ መስራትህን ቀጥል።


ያኔ ልማት ተስፋ ብቻ ሳይሆን እውነታ ይሆናል።


በባስሬ ባልቻ

የካቲት 11/2018 ዓ.ም

 
 
 

Comments


bottom of page